“የዐይን እማኝ!”

ፖፑሌሽን ሚዲያ ሴንተር ኢትዮጵያ መንግሥታዊ ያልሆነ ዓለምአቀፋዊ ተቋም ሲሆን፤ ዋና መሥሪያ ቤቱ በአሜሪካ ቬርሞን ይገኛል። የዚህ ድርጅት ፕሮጀክቶች በማኅበራዊ ለውጥና ዕድገት ላይ ያተኮሩ ሲሆን፤ በኢትዮጵያ ባለፉት ከ20 ዓመታት በላይ ጥናትና ምርምርን መሠረት ባደረጉ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ተግባራት፣ አሳሳቢ የሆኑ የሀገራችንን የጤናና ማኅበራዊ ችግሮች ለመፍታት ከሚመለከታቸው አጋር ድርጅቶችና መንግሥታዊ ተቋማት ጋር በመተባበር ሲሰራ የቆየ፤ አሁንም በመሥራት ላይ የሚገኝ ድርጅት ነው።

ፖፑሌሽን ሚዲያ ሴንተር ኢትዮጵያ በሥነ ተዋልዶ ጤና÷ በተለይም በቤተሰብ ዕቅድ፣ ኤች አይቪ/ኤድስ መከላከል፣ የሕፃናት ጋብቻ፣ የሴት ልጅ ግርዛትና ሌሎች ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች አሳሳቢነት በተመለከተ በሕብረተሰቡ ዘንድ ተገቢው ግንዛቤ እንዲፈጠርና የባሕርይ ለውጥ እንዲመጣ ሀገር አቀፍ አስተዋጽኦ ያደረጉ በርካታ ሥራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል።     

ፖፑሌሽን ሚዲያ ሴንተር ኢትዮጵያ በብዙዎች ዘንድ የሚታወቀው  በሚያቀርባቸው ተከታታይ የራድዮ ድራማዎቹ ሲሆን፣ ዕውቀትን በማሳደግ ሕብረተሰቡ በጎጂ ድርጊቶች ላይ ያለውን የተሳሳተ አመለካከት   በመለወጡ ረገድ ስኬታማ ትሩፋቶችን ተጎናጽፏል። በኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ በጣም ተወዳጅ የሆኑት “የቀን ቅኝት”፣ “ድምቢባ”፣ “ማለዳ”፣ “መንታ መንገድ”፣ “ስብራት” “ምዕራፍ”፣ እና “ንቃቃት” የተባሉት ተከታታይ የራድዮ ድራማዎች በቤተሰብ ዕቅድ፣ በኤች አይ ቪ/ኤድስ፣ በጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች በተለይም የሴት ልጅ ግርዛትና፣ የሕፃናት ጋብቻን መከላከል፣ ሥርዓተ ፆታና የፆታ ጥቃቶች፣ በወጣቶች ሥነ-ምግባር፣ በሴቶች አቅም ማጎልበት ላይ ያተኮሩ ነበሩ።      ፖፑሌሽን ሚዲያ ሴንተር ኢትዮጵያ ከተለያዩ ዓለም አቀፍና ሀገር አቀፍ ድርጅቶች ጋር በመተባበር በተለያዩ ከሚዲያ ሥራዎች ጋር የተገናኙ የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎችን ሲያከናውን የቆየ ሲሆን፤ በተጨማሪም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሲኤፍ) ጋር በመተባበር ከአካባቢ ንጽህና/ሃይጂን፣ ከንጹህ ውሃ አቅርቦት እና ከግል ንጽህና ጋራ የተያያዙ የማስተማሪያ ማኑዋሎችን በማዘጋጀት÷ ለሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት እንዲደርስ የበኩሉን አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ ይገኛል።  

በተከታታይ የራድዮ ድራማዎች፣ ቶክሾውና የኅትመት ሥራዎችን በማቅረብ የሚታወቀው ይህ ድርጅት፣ በተለይ በሕትመት ውጤቶችም ተደራሽ ለመሆን በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ በርካታ መጽሐፍትን በማሳተም ሚሊዮኖች እንዲያነቡ አስችሏል። ከነዚህም መካከል የሕይወት ጠብታዎች፣ ክንፋም ሕልሞች፣ ዛሬን ከተጉበት፣ ወንዞች እስኪሞሉ፣ የማለዳ ሸክም፣ ያልተናበቡ ልቦች፣ ውርስ፣ ሙሉ ሰው፣ የኔዓለም፣ አዙሪት፣ ታጋቾች፣ አለኝታ ተከታታይ መጽሔቶች፣ ብለድ ፕራይስ (Blood Price)፣ ዲችድ ኢን ዘ ጃንግል (Ditched in the Jungle) እና ሌሎችም ይጠቀሳሉ።

ለዛሬ በዚህ ጽሑፍ ለማቅረብ የወደድነው “የዐይን እማኝ” የተሰኘ መጽሐፉ ሲሆን፤ መጽሐፉ እውነተኛ ታሪኮችን ይዟል። ይህ መጽሐፍ የሴት ልጅ ግርዛት፣ የሕፃናት ጋብቻ፣ የቤተሰብ ምጣኔ እና ፆታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች የሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጓል። የዐይን እማኝ መጽሐፍ፣ በእውነተኛ የሕይወት ገጠመኞች ላይ የተመሠረቱ 10 የተለያዩ ታሪኮችን ይዟል።  ደራስያኑም በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ተዘዋውረው የተለያዩ የመስክ ምልከታዎችን በማድረግና ማስረጃዎችን በማሰባሰብ እውነተኛ ታሪኮቹን እንዲጽፉ ተደርጓል። መጽሐፉ የሴቶችና የሕፃናትን አስቸጋሪ የኑሮ ውጣውረዶችን እና የወሰዷቸውን እርምጃዎች በግልጽ የሚያሳዩ እውነተኛና መሳጭ ታሪኮችን ይዟል። ፖፑሌሽን ሚዲያ ሴንተር ኢትዮጵያ መጽሐፉን ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሥነ ሕዝብ ፈንድ (ዩኤን ኤፍ ፒ ኤ) እና ከካናዳ መንግሥት በተገኘው የገንዘብ ድጋፍ ስመጥር ጸሐፍትና ደራሲያንን በማሳተፍ አሳትሞ ለተለያዩ የመንግሥት ተቋማት፣ ለለጋሽ ድርጅቶች፣ ለማረሚያ ቤቶች፣ ለተጽዕኖ  ፈጣሪና በጉዳዩ ላይ ለሚሰሩ ግለሰቦች፣ ፖፑሌሽን ሚዲያ ሴንተር ኢትዮጵያ በተለያዩ ወረዳዎች ላደራጃቸው የራድዮ አድማጭ ቡድኖች፣ ለልማት ማሕበራት፣ ለትምህርት ቤቶችና ለሌሎችም አሰራጭቷል።

ታሪካቸው በመጽሐፉ የተካተቱ ሴት ልጃገረዶች እውነተኛ ታሪካቸውን ያጋሩ ሲሆን፤ በፖፑሌሽን ሚዲያ ሴንተር ኢትዮጵያ አማካኝነት ተዘጋጅቶ በቀረበው “ንቃቃት” በተሰኘው ተከታታይ የራድዮ ድራማ አማካኝነት ግንዛቤ አግኝተው የተፈጸመባቸው ድርጊት የሴቶችና የሕፃናትን ሰብዓዊ መብት የሚጥስ በመሆኑ አፋጣኝ መፍትሔ እንዲያገኝ ፊትለፊት የሞገቱ ናቸው።  “ንቃቃት” የራድዮ ድራማ በመከታተላቸው ሞጋች እና የጉዳዩ የመፍትሔ አካል የሆኑ ወጣቶችን ማፍራት መቻሉን ከመጽሐፉ የተወሰደች የታዳምቅ ጤናውን የደብዳቤ ይዘት ቀንጨብ አድርገን አቅርበነዋል።

ቀን 02/06/2014 ዓ.ም

ለልጃገረዶች ክበብ

ጉዳዩ፡- ክስ ስለመመሥረት!

“እኔ ታዳምቅ ጤናው በጃይካ ት/ቤት የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ መሆኔ ይታወቃል። በት/ቤት ቆይታዬ በተለያዩ ክበባት ተሳትፎ በማድረግ የተለያዩ ዕውቀቶችን ገብይቻለሁ። በተለይም በልጃገረዶች ክበብ በነበረኝ ተሳትፎ የቀሰምኩትን መነሻ በማድረግ የበርካታ እህቶቼን ያለ ዕድሜ ጋብቻ ለማስቀረት በሚደረገው ጥቆማና ሥልጠና የነቃ ተሳትፎ አድርጊያለሁ። የፈሩት ይደርሳል የጠሉት ይወርሳል- ሆነና ቤተሰቦቼ ያለ ዕድሜዬ እኔን በዐሥራ አራት ዓመቴ ሊድሩኝ፣ ታናሽ እህቴን ደግሞ በዐሥራ ሦስት ዓመቷ ሊድሯት መሆኑን ቀደም ብሎ መረጃ ከደረሰኝ በኋላ እንዲቀር ቤተሰቦቼን ብጠይቅም የሚሰማኝ አጣሁ። ስለሆነም የምወደውና የምጓጓለት ትምህርቴ መና እንዳይቀር ት/ቤቴ ወላጆቼን ለመክሰስ በማደርገው እንቅስቃሴ ሁሉ ከጎኔ እንዲሆን በትሕትና እጠይቃለሁ። እወዳችዋለሁ።”

ከሠላምታ ጋር!

ፊርማ

ተማሪ ታዳምቅ ጤናው

በትምህርት ቤቱ ዳይሬክተር አማካኝነት ደብዳቤው ለልጃገረዶች ክበብ ገቢ ሆነ። ከተለያዩ ክፍሎች የተውጣጡ አካላት እንዲሳተፉበት እና ጉዳዩን እንዲያውቁት ተደረገ። በቀጣይም ለጎዛመን ወረዳ ሴቶችና ሕፃናት ጽህፈት ቤት በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ ተሰጠ። ለጊዜው ሴቶችና ሕፃናት ጽህፈት ቤት ለእነራታ ቀበሌ አስተዳደር ጉዳዩን እንዲያስቆም ደብዳቤ ፃፈ። በተደረገም ጥረትም የታዳምቅና ታናሽ እህቷ ያለዕድሜ ጋብቻው እንዲሰረዝ ተደርጓል። ሙሉውን መሳጭ ታሪክ የ”ዐይን እማኝ” ከተሰኘው የእውነተኛ ታሪኮች መድብል ያገኙታል።   

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *