በእሷ እና በወደፊት ሕይወቷ መካከል ያሉትን መሰናክሎች እናስወግድ!

እ.ኤ.አ በ1954 በወጣውና በ1959 በፀደቀው ዓለም አቀፍ የወጣት ሴቶች መብቶች ድንጋጌ ላይ ለሕፃናት ልዩ
እንክብካቤና እርዳታ ማድረግ የቤተሰብም የማሕበረሰብም ግዴታ መሆኑ በግልፅ ተቀምጧል፡፡

ኦክቶበር 11 የዓለም ወጣት ሴቶች ቀን ሆኖ እ.ኤ.አ
ከ2012 ጀምሮ እንዲከበር የተባበሩት መንግሥታት
ጠቅላላ ጉባዔ ያሳለፈውን ውሳኔ ተከትሎ በዓሉ
በመከበር ላይ የሚገኝ ታላቅ ዓለም አቀፍ ኩነት
ሲሆን፤ ዘንድሮም በዓለም አቀፍ ደረጃ Invest in Girls' Rights: Our Leadership, Our Well- being “በወጣት ሴቶች መብት ላይ መስራት ጥቅሙ
የጋራ ነው፤ አመራራችን ለሁለንተናዊ ደህንነት” በሚል መሪ ቃል በዓሉ ተከብሮ ውሏል። ታዳጊ ሕፃናት በጾታቸው ምክንያት ከሚደርስባቸው
መድሎና መገለል፣ ከኃይል ጥቃት፣ በታዳጊነት
ከሚፈጸም ጋብቻና የሴት ልጅ ግርዛት ከመሳሰሉ ጎጂ ድርጊቶች እንዲጠበቁ እንዲሁም የጤና፣ ትምህርትና ሌሎች አገልግሎቶች ተደራሽ እንዲሆኑ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ተገቢ ነው።

ሴት ሕፃናት ከቤተሰብ ጀምሮ፣ በማሕበረሰብና በሀገር ደረጃ አቅማቸውን ያገናዘቡ ተሳትፎዎችን ማድረግና ተጽዕኖ መፍጠር እንደሚችሉ ይታመናል። ይህ ዕለት መከበሩ ሕፃናት ችግሮቻቸው እንዲፈቱላቸውና መብቶቻቸው እንዲከበርላቸው ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ማሰማት የሚችሉበትን መልካም አጋጣሚ ፈጥሯል።

ሆኖም እያንዳንዷ ወጣት ልጅ የትም ብትሆን ስለ መብቷ በደንብ ጠንቅቃ በማወቅ፣ ትምህርቷን በአግባቡ እንድትከታተል ፣ የጤና እንክብካቤ እንድታገኝ፣ ያለምንም ጥቃት እንድታድግ መሥራት የሁሉም አካል ድርሻ ነው። በጾታዊ እና በሥነ ተዋልዶ ጤና አገልግሎቶችን መሠረት ያደረጉ ኢንቨስትመንቶች መጨመር እና በአፍላነት ዕድሜ ላይ ያሉ ልጃገረዶች ስለ ሰውነታቸው እና ሕይወታቸው በመረጃ ላይ የተመሠረተ ውሳኔ እንዲወስኑ እንዲሁም የለውጥ አራማጆች እና የወደፊት መሪዎች እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል።

በኢትዮጵያ የወጣት ሴቶች ዝውውር አንዱና ዋነኛው የማህበራዊ ችግር ነው። ይህ ችግር በድህነት መስፋፋት እና በህገወጥ አዘዋዋሪዎች ሕጻናትንና ታዳጊ ወጣቶችን በከፍተኛ ሁኔታ በመጉዳት ላይ ይገኛል። በተጨማሪም በህገወጥ መንገድ የሚዘዋወሩ ህፃናት አካላዊ እና ስሜታዊ ጥቃቶች እንደሚደርስባቸው ይታወቃል – መደፈር፣ ረሃብ፣ አካላዊ ጥቃት፣ አካል መጉደል፣ የጤና መታወክ እና ይብስ እስከ ሞት ሊያደርስ ይችላል።

ብዙ ጊዜ ወጣት ሴቶችን ለጉልበት ብዝበዛ ተጋላጭ ከሚያደርጓቸው ምክንያቶች ድህነት በቀዳሚነት ተጠቃሽ ነው። ብዙ ደሃ ቤተሰቦች ኑሯቸውን ለመደጎም ሲሉ ለስራ ያልደረሱ ወጣት ሴቶችን የተለያዩ ስራዎችን እንዲያከናዉኑና ለቤተሰቡ ተጨማሪ ገቢ እንዲያስገኙላቸዉ ይጥራሉ። ወጣት ሴቶችን ለጉልበት ብዝበዛ የሚያጋልጣቸው ሌላው ምክንያት ከባህላችንና ከልምዳችን ጋር የተያያዘ ነው። አብዛኛው ሰው ወጣት ሴቶችን በለጋ ዕድሜያቸው የተለያዩ ዕውቀቶችና ክህሎቶች እንዲኖራቸው በማሰብ በስራ ላይ እንዲሰማሩ ይደግፋሉ ይገፋፋሉም። የትምህርት ዕድል ያለመኖርም፣ የወላጆች ሞት፣ በቂ የገቢ ምንጭ አለመኖር፣ የወላጆች የትምህርት ደረጃ ማነስ፣ የቤተሰብ መፍረስ፣ ግጭትና የቤት ውስጥ ጥቃቶች የመሳሰሉትም በመንስኤነት ሊጠቀሱ ይችላሉ።

ወጣት ሴቶች ጉልበት ብዝበዛ በህፃናቱ ላይ ከሚያሰከትለው ከፍተኛ የአካላዊ፣ ስነልቦናዊ፣ ማህበራዊና የመሳሰሉት ጉዳቶች ባለፈ በህብረተሰብና በሀገር ላይ የሚያስከትለው ጉዳት ከፍተኛ ነው። የብዝበዛው ሰለባ የሆኑ አፍላ ሴቶች ከቀላል የአካል ጉዳት እስከ ሞት ለሚደርስ ጉዳት ይጋለጣሉ ወይም ለዕድሜ ልክ ለማይሽር አካላዊም ሆነ አእምሯዊ ጉዳት ሊዳረጉ ይችላሉ። የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ የሀገር ኢኮኖሚ ላይም አሉታዊ ተፅእኖ ያስከትላል። ከድህነት ጋር በተያያዙና በልዩ ልዩ ምክንያቶች በሀገር ውስጥም ሆነ ወደ ውጭ በሚደረገው የህገወጥ የሕፃናት ዝውውር የወደፊት ሀገር ተረካቢ ሊሆን የሚችለውን በርካታ አምራችና ብቁ የሰው ኃይል ማጣትን ሊያስከትል ይችላል።

ፖሌሽን ሚዲያ ሴንተር ኢትዮጵያ በተለያዩ የሀገሪቷ ክልሎች የሴት ልጆች ጤናማና ብሩህ የወደፊት ሕይወት ለመፍጠር ከአጋሮቹ ጋር በመሆን የተለያዩ ተግባራትን በማከናወን ላይ ይገኛል። ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሥነ ሕዝብ ፈንድ (ዩኤንኤፍፒኤ) ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሕፃናት ፈንድ (ዩኒሴፍ) እና ከዓለም አቀፍ የሕፃናት አድን ድርጅት (ሴቭ ዘ ቺልድረን) ጋር ጾታዊ ጥቃትን፣ በታዳጊነት የሚፈጸም ጋብቻን እና የሴት ልጅ ግርዛትን ለማስቆም፣ ለሴቶች ልጆች የሕይወት ክህሎት ሥልጠና በመሥጠት፣ የሥነ ተዋልዶ ጤና አገልግሎቶችን በማስትዋወቅ፣ የሕጻናት ዝውውር እና ጉልበት ብዝበዛ እና ሌሎች ሰብዓዊ መብትን የሚጋፉ/የሚጥሱ ድርጊቶችን በመቃወም ህብረተሰቡን የሚያስተምሩና የሚያነቃቁ በራድዮ የሚተላለፉ በርካታ ተከታታይ ድራማዎችንና የሬድዮ ፕሮግራሞችን በማዘጋጀት፣ የህትመት ወጤቶችን በማሰራጨት፣ ስልጠናዎችን በመስጠት፣ ለሕጻናትና ወጣት ሴቶች የተለያዩ ደጋፎችን በማድረግ እንዲሁም ማህበራዊ ሚዲያዎችን በመጠቀም በርካታ የሃገራችን ክልሎች ላይ እየሰራ ይገኛል።

በታዳጊነት የሚፈጸም ጋብቻንና የሴት ልጅ ግርዛትን ማስቀረት፣ ጥቅሙ ጤናን እና ሰብአዊ መብቶችን ከማስጠበቅ ያለፈ ነው። የተሻሉ የትምህርት ፖሊሲዎች እና ውጤቶች ወጣት ሴቶች በመደበኛው ኢኮኖሚ ውስጥ ሥራ እንዲያገኙ እና ለቤተሰቦቻቸው የበለጠ ውጤታማ የሆነ አስተዋፅዖ እንዲያበረክቱ ዕድል ይሰጣቸዋል። የ2030 ለዘላቂ ልማት ግቦች ቀነ ገደብ በመቃረቡ እያንዳንዷ በአፍላ ዕድሜ ላይ የምትገኝ ልጃገረድ በሁሉም ልዩነት ውስጥ መብቷን እና ምርጫዋን እንድትጠቀም፤ አቅሟንም ሙሉ በሙሉ እንድትገነዘብ እንዲሁም ለራሷ የምታስበውን የወደፊት ጊዜ እንድትገነባ የበኩላችንን እንወጣ። ከማሕበረሰብ ጋር ጥብቅ ግንኙነት ያላቸውን ወጣት ሴቶች በመፍጠር ጤናማ የሆነ ዜጋን ከማፍራት አኳያ ተቋማችንም ኃላፊነቱን በመወጣት ላይ ይገኛል። በመሆኑም “የአንድ ልጅ መደገፍ የሀገር መደገፍ” መሆኑን ተገንዝበን ሁላችንም የበኩላችንን ኃላፊነት እንድንወጣ አደራ ለማለት እንወዳለን፡፡

“በእሷ እና በወደፊት ሕይወቷ መካከል ያሉትን መሰናክሎች እናስወግድ!” የፖፑሌሽን ሚዲያ ሴንተር ኢትዮጵያ የወሩ መልዕክት ነው!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *