ወጣት ሴቶች የጀመሩትን ትምህርት እንዳያቋርጡ እናበረታታቸው!!
በዓለም አቀፍ ደረጃ ከስድስት እስከ 18 ዓመት ዕድሜ ያላቸው 244 ሚሊዮን ሕፃናት ከትምህርት ገበታቸው ውጪ መሆናቸውን የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) እአአ 2022 ያወጣው መረጃ ያመለክታል። ከዚህ ውስጥ ክፍተኛው ቁጥር የተመዘገበው ከሰሃራ በታች ባሉ ሀገራት ሲሆን፤ 50 ሚሊዮን የሚሆኑት ሴት ልጃገረዶች ትምህርታቸውን አቋርጠዋል። ይህ ከሌሎች አህጉሮች ከትምህርት ቤት ውጭ ካሉ ልጃገረዶች በእጅጉ የሚበልጥ አኅዝ ሲሆን፤ ቁጥሩም እያደገ መምጣቱን ያሳያል። እነዚህም አብዛኞቹ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው ሀገራት የሚኖሩ ናቸው።
ፓፑሌሽን ሚዲያ ሴንተር ከተባበሩት መንግሥት ሕፃናት መርጃ ድርጅት (ዮኒሴፍ) ጋር በመተባበር በተመረጡ የገጠር ወረዳዎች ለጉዳዮ ትኩረት በመስጠት ችግሩን ለመቅረፍ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡ ለልጃገረዶች ሌሎች ተማሪዎችና መምህራን እንደዚሁም ለማህበረሰብ አባላት ስለወር አበባ ጤናና አጠባባቅ ያላቸው ግንዛቤ እንዲጨምር በተለይም በዚህ የተነሳ ወጣት ልጃገረዶች ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና በመስጠት የአቅም ግንባታና ሙያዊ ክህሎት እንዲያገኙ እገዛ እየተደረገላቸው ይገኛል፡፡ በተደጋጋሚ ሊጥቀሙበት የሚችሏቸውን የግል ንፅሕና መጠበቂያ በአከባቢያቸው ከሚገኙ ቁሳቁስ በተለይም የሴቶች የውስጥ ሱሪ (ፓንት) እና ሞዴስ እንዴት በቀላሉ ማዘጋጀት እንደሚቻል፣ ከተጠቀሙ በኋላም በቀላሉ በማጠብ በተደጋጋሚ ጥቅም ላይ ማዘጋጀት እንደሚቻል በሥልጠናው ውስጥ በማካተት በርካታ ሴት ልጃገረዶችን ለማገዝ እየተሞከረ ነው፡፡ በዚህ ሥልጠና የተሳተፉ ሴት ልጃገረዶች ያገኙትን ክህሎት ለሌሎች በማስተላለፍ በየት/ቤታቸው ለሚገኙ ማህበረሰብ በማስተዋወቅ ጉዳዮ ተግባራዊ እንዲሆንና ተቀባይነት እንዲኖረው በማድረግ ላይ ይገኛሉ::