ከፖፑሌሽን ሚዲያ ሴንተር የሥነ-ሕዝብ ዕድገትና እንድምታው

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) እስከ አውሮፓውያኑ 2030 ድረስ ለማሳካት በልማት ግብነት ከያዛቸው አጀንዳዎች መካከል ዋነኞቹ የሴቶችን የሥነተዋልዶ ጤና ማዳረስ፤ የወሊድ መከላከያ የሚጠቀሙ እናቶችን ቁጥር የማበራከት እንዲሁም በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ ላለው የሕዝብ ቁጥር መፍትሔ ማበጀት የሚሉት ይጠቀሳሉ። በፍጥነት እየጨመረ የመጣውን የዓለም የሕዝብ ብዛት ለመቆጣጠር ለሚከናወኑ ተግባራት ላለፉት 50 ዓመታት የገንዘብ አቅርቦት የሚያደርገው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሥነ-ሕዝብ ፈንድ (ዩኤንኤፍፒኤ) በዓመት 1.3 ቢሊየን ዶላር በጀት ለዚህ ዓላማ እንዲውል ያደርጋል።  

በዓለም አቀፍ ደረጃ በጉዳዩ አሳሳቢነት ላይ ለመምከርና የመፍትሔ አቅጣጫ ለማስቀመጥ እ.አ.አ በየዓመቱ ጁላይ 11 ዓለም አቀፍ የሥነ-የሕዝብ ቀን በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ በመምከር ይታሰባል። በያዝነውም ዓመት  (ማንንም አትተዉ ሁሉም ግምት ውስጥ ይግቡ”) በሚል መሪ ቃል ቀኑ ታስቦ ውሏል። ይህ ዓለም አቀፍ የሥነ-ሕዝብ ቀን መድረክ ትኩረት ከሚያደረግባቸው ርዕሰ ጉዳዮች በዋናነት ለፆታዊ እና ለሥነ-ተዋልዶ ጤና አገልግሎት ያለው ተደራሽነት ማሳደግ፣ የተመድ የሥነ-ሕዝብ የገንዘብ ድጋፍን ዓላማዎች በማሳካት ረገድ የገንዘብ ምንጮችን የመለየት፤ የሕዝብ ብዛትና ስብጥርን ከኤኮኖሚ ዕድገት፣ ጥንካሬ እና ከዘላቂ ልማት ስኬት አኳያ መጠቀም፣ ፆታን መሠረት ያደረገ ጥቃት እና የሴት ልጅ ግርዛት የመሳሰሉ ጎጂ ድርጊቶችን ማስቆም፤ ሰብዓዊ ቀውስ እና አስጊ ሁኔታ ባለበት ሳይቀር የፆታ መብት እና የሥነ-ተዋልዶ ጤና መብትን መጠበቅ የሚሉ እንደ መወያያ ርዕሰ ጉዳዮች ይዳሰሱበታል።  የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው በየዓመቱ 90 ሚሊየን የሚሆኑ ሴቶች ያለእቅድ እንደሚፀንሱ እና ከሦስት ሴቶች አንዷ ፆታዊ ጥቃት ይደርስባታል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (የተመድ) መረጃ እንደሚያሳየው ደግሞ የሕዝብ ቁጥር መጨመር በሥራ፣ በኢኮኖሚ ልማት፣ በድኅነት፣ በገቢ ክፍፍል እና በማኅበራዊ ጥበቃ ላይ ተጽእኖ ያሳድራል። የቤተሰብ ምጣኔ በ2030 በሚፈለገው ልክ እንዲሳካ ሦስት ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት ያስፈልጋል። ከወሊድ ጋር የትርያያዘ  ሞትን ዜሮ ማድረግ፤ በእያንዳንዷ ቀን ከወሊድ (ከእርግዝና) ጋር በተያያዘ የሴቶች (የእናቶችን) ሞት ዜሮ እንዲሆን በትኩረት መሥራት፤ እንዲሁም ፆታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች እና በሴቶች እና ልጃገረዶች ላይ የሚፈጸሙ ጎጂ ድርጊቶችን ዜሮ ማድረስ ማስቻል የሚሉት ናቸው።  እ.አ.አ በ2021 የወጡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በኢትዮጵያ  የቤተሰብ ምጣኔ (የወሊድ መቆጣጠሪያ) የሚጠቀሙ ሴቶች (እናቶች) 36 በመቶ  የነበረ ሲሆን፤ በአሁኑ ጊዜ ቁጥሩ ከፍ እንደሚል ይገመታል። ከዚህ በተጨማሪ የቤተሰብ ዕቅድ መጠቀም እየፈለጉ  መጠቀም ያልቻሉ ሴቶች ቁጥር 22 በመቶ በመሆኑ ሊታሰብበት ይገባል። ያልተሟላውን ፍላጎት ለማዳረስ ከመንግሥትና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በቅንጅት መሥራት አስፈላጊ መሆኑን ፖፑሌሽን ሚዲያ ሴንተር ያምናል።

የፖፑሌሽን ሚዲያ ሴንተር መሥራችና ፕሬዚዳንት እንዲሁም ላለፉት ሃያ አምስት ዓመታት በላይ በሥነ-ሕዝብና የሥነ-ተዋልዶ ጤና ላይ የካበተ ልምድ ያላቸው ቢል ራይርሰን በአንድ ወቅት ቲአርቲ ከተባለ ዓለም አቀፍ ቴሌቭዥን ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ የቤተሰብ ምጣኔ እና የሥነ-ተዋልዶ ጤና ወሳኝ ናቸው።  ውጤታማ የቤተሰብ ምጣኔ ለጤና አገልግሎት፣ ለኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት፣ አከባቢያዊ እንዲሁም ማሕበራዊ ጠቀሜታዎች እንዳሉት ገልጸው ነበር።  ከዚህም በተጨማሪ “ቤተሰብን መመጠን የልጆቻቸውን ቁጥር እና መሠረታዊ ፍላጎቶቻቸው እንዲሟላላቸው ከማስቻሉም ባሻገር ተገቢው የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ፣ ብሎም ለአዕምሮ ዕድገታቸውም ሚናው የጎላ ይሆናል” ባይ ናቸው ፕሬዚዳንቱ። እንደ ቢል ራይርሰን ኃሳብ ቤተሰብን መመጠን የተመጣጠነና የተሻለ ኢኮኖሚ ዕድገት እንዲመዘገብ ያስችላል። ለዚህም ፖፑሌሽን ሚዲያ ሴንተር ባለፉት 25 ዓመታት በሥነ-ሕዝብ፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ በቤተሰብ ምጣኔ እና ጤናማ ሥነ-ተዋልዶ እንዲሁም በማሕበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ በአዝናኝ እና ትምህርታዊ የራድዮ ፕሮግራሞቹ አማካኝነት ስኬታማ ሥራዎችን መሥራቱን ቢል ገልጸዋል።  በያዝነው በጀት ዓመት ፖፑሌሽን ሚዲያ ሴንተር-ኢትዮጵያ ከዲኬቲ ጋር በመተባበር በሀገሪቱ በአምስት ክልሎች የወጣቶች የሥነ-ተዋልዶ ጤና፣ በቤተሰብ ምጣኔ፣ ፆታዊ ጥቃትን መከላከል እንዲሁም በማሕበራዊ ትስስር /የሠላም ግንባታ) ላይ ለመሥራት በእንቅስቃሴ ላይ ይገኛል።    

እ.አ.አ በ1989 የዓለም የሕዝብ ብዛት 5 ቢሊዮን በመድረሱ ያሳሰበው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም (ዩኤንዲፒ) ቀኑ በየዓመቱ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች እንዲመከርበት እና በትኩረት እንዲሰራበት ጁላይ 11 ዓለም አቀፍ የሥነ-ሕዝብ ቀን  ታስቦ እንዲውል ወስኗል። ኢትዮጵያም የሥነ-ሕዝብ ፖሊሲ ተግባር ላይ ማዋል ከጀመረችው እ.አ.አ ከ1993 ጀምሮ ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥታ የተለያዩ ተግባራትን በማከናወን ላይ ትገኛለች።  #PopulationMediaCenter #SustainableFuture

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *