“መቼም፣ የትም፣ በምንም ሁኔታ ፆታዊ ጥቃትን ዝም አንበል!”

እ.ኤ.አ በ2016 በኢትዮጵያ በተካሄደው የሥነ ሕዝብ እና የጤና የዳሰሳ ጥናት (EDHS) እንደሚያሳየው 33 በመቶ የሚሆኑት ዕድሜያቸው ከ15-49 የሆኑ ሴቶች ወሲባዊ ወይም አካላዊ ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል። ጥናቱ እንደሚያሳየው፣ በዚሁ ዕድሜ ክልል ውስጥ ካሉ ሴቶች ውስጥ 10 በመቶ የሚሆኑት ወሲባዊ ጥቃት ሲፈጸምባቸው፤ 23 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ካላዊ ጥቃትን አስተናግደዋል። በተመሳሳይ ከአራት ሴቶች ውስጥ አንዷ ከ15 ዓመቷ ጀምሮ ጾታዊ ጥቃት ያጋጥማታል።

ዓለም አቀፍ የ16 ቀናት እንቅስቃሴ፣ በሥርዓተ-ፆታ ላይ የተመሰረተ ጥቃትን ለመከላከልና ለማስቀረት በዓለም አቀፍ ደራጃ ለ32ኛ ጊዜ “በሴቶችና ልጃገረዶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለመከላከል ኢንቨስት ያድርጉ!” በኢትዮጵያ ደግሞ ለ18ኛ ጊዜ ‘መቼም፣ የትም፣ በምንም ሁኔታ ፆታዊ ጥቃትን ዝም አንበል!”’ በሚል መሪ ኃሳብ ለተከታታይ ሁለት ሳምንታት መከበር ጀምሯል። ዘመቻው በሴቶችና ልጃገረዶች ላይ የሚደርሰው ጥቃት እንዲቆም ጥሪ ለማቅረብ የታለመ ሲሆን፤ ከሕዳር 18 እስከ ታኅሳሣሥ 1 ቀን 2016 ዓ.ም የሚቆይ ይሆናል።

ፆታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች በማሕበረሰቡ ውስጥ ያለውን የተዛባ ፆታዊ
የግንኙነት ሁናቴ መገለጫ ነው። ይህ ድርጊት ቀዳሚና ዋንኛው የሰብዓዊ
መብት ጥሰት ሲሆን፤ የትም ይከሰት የትም ፆታዊ ጥቃት ለፆታዊ እኩልነት
መረጋገጥ፤ ለሕብረተሰብ ጤና፣ በሀገር ልማትና እድገትም ላይ ከፍተኛ ስጋት
የሚጥል እና ቀጣይነት ያለው የልማት፣ የኢኮኖሚ፣ የሠላም እና የእድገት
እንቅፋት ነው። ሴቶችና ልጃገረዶች ደህንነት የማይሰማቸው ከሆነ
በማሕበረሰባቸው ልማትና እድገት ላይም ሙሉ ተሳትፎ አይኖራቸውም።
በኢትዮጵያ ጾታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች ትኩረት የሚሹ ዋንኛ ጉዳዮች
ናቸው። የትዳር አጋሮች ጥቃት፣ ወሲባዊ ትንኮሳና ጥቃት፣ የሴት ልጅ
ግርዛት፤ በጠለፋ የሚደረግ ጋብቻ፤ አስገድዶ መድፈር እና ያለዕድሜ ጋብቻ
በብዛት ከሚታዩ የፆታዊ ጥቃት ዓይነቶች ናቸው። በሴቶች ላይ የሚደርሱ
እነዚህን መሰል ጥቃቶች በግለሰብ ደረጃ የሚደረጉ ፆታዊ ጥቃቶች ሲሆኑ፤
የሀገሪቱን ማሕበረሰባዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት የሚያበላሹ ድርጊቶች
ናቸው። በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ስምምነቶች ፆታዊ ጥቃት መሰረታዊ የሰው
ልጆች መብት ጥሰት መሆኑ ተደንግጓል። በሴቶች ላይ የሚደረግ ጾታን
መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች ሴቶች መብቶቻቸውን እንዳይጠቀሙ
ያግዳቸዋልድ። በሴቶች ላይ የሚፈፀም ጥቃት በተለምዶ በወንዶች
የሚፈጸም ነው። በሴቶች ላይ የሚፈጸም ጥቃት በወንዶች ካልተመጣጠነ የበላይነት (ሥልጣን) ግንኙነት ይመነጫል። የተለያዩ ዓይነት የበላይነቶች አሉ፤ እንደ ኢኮኖሚ የበላይነት (ገንዘብ እና ሌሎች ምንጮችን መቆጣጠር) እና አካላዊ የበላይነት (የአካል ጥንካሬ ወይም መሣሪያ መጠቀም) ጥቂቶቹ ናቸው። በማሕበረሰቡ ዘንድ ሴቶች ከወንዶች ይልቅ የበታች ናቸው። የበታች የሆኑ ሴቶች ደግሞ በብዙ መልኩ ለጥቃት
ተጋላጮች ናቸው።

የፆታ እኩልነት የሚረጋገጠው ሁሉም የሰው ልጆች እኩል መብት ሲያገኙ መልካም የሕይወት አጋጣሚ ሲፈጠርላቸውና የአኗኗር ዘይቤያቸውን ለማስተካከል ሙሉ መብት የተሰጣቸው ከሆነና ለማሕበረሰቡ አስተዋጽኦ ማድረግ ሲችሉ ነው። ከዚህ በተቃራኒው የፆታ እኩልነት አለመከበር ደግሞ ያልተመጣጠነ የኃይል ሚዛንና ፆታን መሠረት ያደረገ ማግለል የፆታዊ ጥቃት ናቸው። ይህ ደግሞ የፆታዊ እኩልነት መረጋገጥ ዋንኛ እንቅፋት ሲሆን፤ ያልተመጣጠነ የኃይል ሚዛን ደግሞ ጾታን መሠረት አድርገው የሚመጡ ናቸው።

ፖፕሌሽን ሚዲያ ሴንተር ኢትዮጵያ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት
የሥነ ሕዝብ ፈንድ (ዩኤንኤፍፒኤ)፣ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዓለም አቀፍ የሕፃናት ፈንድ (ዩኒሴፍ)፣ ከዓለም አቀፍ የሕፃናት አድን ድርጅት (ሴቭ ዘ ቺልድረን፣ እና ከሌሎች አጋሮች በሚያገኘው የገንዘብ ድጋፍ እነዚህ በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ለመከላከል የተለያዩ ትምህርታዊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን ሲሰራ ቆይቷል። በሀገሪቱ በአንዳንድ አካባቢዎች አሁንም በጎጂ ድርጊቶች ላይ የተዛባ አመለካከቶች ያሉ በመሆኑ፤ የችግሩን አሳሳቢነት ከሥሩ ለመፍታት የሚያስችል ሥልቶችን በመንደፍ በመሥራት ላይ ይገኛል። ችግሮቹንም ለመፍታት ፖፕሌሽን ሚዲያ ሴንተር ኢትዮጵያ
እየሰራቸው ካሉ ተግባራት መካከል በጉዳዩ ላይ ያተኮሩ የራዲዮ ፕሮግራሞች፣ የተለያዩ የንቅናቄ ሥራዎች፣ የተለያዩ የተግባቦት ሕትመቶች ማሳተም እና ማሰራጨት፣ የትምህር ቤት ሚኒ ሚዲያዎችን በመጠቀም ቁልፍ መልዕክቶችን ማስተላለፍ፤ የራዲዮ አድማጭ ቡድኖችን በማቋቋም በጉዳዩ ላይ የተዘጋጁ የራዲዮ ድራማ እና የውይይቶት ፕሮግራሞችን እንዲከታተሉ እና ግንዛቤ እንዲይዙ ሁኔታዎችን የማመቻቸት እና የመሳሰሉት በጥቂቱ ይገኙበታል። በሚሰሩ ሥራዎች የአመለካከት ለውጥ ከማምጣት በተጨማሪ፤ በሴቶችና ሕፃናት ላይ የጾታ ጥቃት እንዳይፈፀም፣ ተፈጽሞም ሲገኝ ተገቢውን ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ በማስቻሉም ረገድ ፖፕሌሽን ሚዲያ ሴንተር ኢትዮጵያ ከሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት እና ሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር በትብብር በመሥራት ላይ ይገኛል።

ስለሆነም በሀገራችን በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚደርሱትን አካላዊ፣ ሥነ ልቦናዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ወሲባዊ ጥቃትም ሆነ ፆታን መሰረት ያደረገ አድልዎን በጋራ መከላከል ‘የሁላችንም ኃላፊነት ሊሆን ይገባል’ የወሩ የፖፕሌሽኝ ሚዲያ ሴንተር ኢትዮጵያ መልዕክት ነው። በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ማውገዝ፣ ተጠቂዎችን መርዳትና መንከባከብ ፣ የተቀናጀና ጥራት ያለው አገልግሎት በመስጠትና ጥቃት የሚፈፅሙትንም በማጋለጥ ለፍትህ ማቅረብ ከኹሉም የሚጠበቅ ኃላፊነት ነው። የፍትህ አካላት፣ ማሕበረሰቡ እና ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት በመስጠትና አፋጣኝ ውሳኔ በማስተላለፍ ወንጀለኞች ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ የኹሉም ኃላፊነቱን መወጣት አለበት።

በያዝነው ሕዳር ለሁለት ሳምንታት በመካሄድ ላይ ያለው እንቅስቃሴ በሴቶች እና ልጃገረዶች ላይ የሚፈፀመውን ፆታዊ ጥቃት ለመከላከል የታለመ ነው። “መቼም፣ የትም፣ በምንም ሁኔታ ፆታዊ ጥቃትን ዝም አንበል!”

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *