ሴቶች እና አካል ጉዳተኞችን ያማከለ የውሃ፣ ሳኒቴሽን እና ኃይጂን (’ዋሽ’) መተግበሪያና ማስፈጸሚያ ሰነዶች ዝግጅት ለማሕበረሰብ ጤናማ ሕይወት
እንደ ኢትዮጵያ በማደግ ላይ ያሉ ሀገሮች ሴቶችና ወጣት ልጃገረዶች የተለያዩ የቤት ውስጥ ሥራዎችን በኃላፊነት ተረክበው የሚሰሩ ሲሆን፤ በአብዛኛው ጊዜ ምግብ ከማብሰል ጀምሮ፣ የቤት ንጽህናን መጠበቅ እንዲሁም ሕፃናትን የማሳደግ ኃላፊነት ይጣልባቸዋል። በገጠራማ አካባቢዎች ደግሞ ረጅም መንገድ በመጓዝ ውሃ የመቅዳት፣ ለማብሰያ የሚውል ማገዶ የመሰብሰብ፣ ከብቶችን የማገድ፣ የእርሻ ሥራዎችን የመሥራት እና የመሳሰሉት ላይ ይሳተፋሉ። በመሆኑም እነዚህ እገዛቸው በቤተሰብ ጤናማ የዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ የጎላ አስተዋጽኦ አላቸው። በተለይም የንጹህ ውሃ አቅርቦት ከፍተኛ ሚና ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው።
የአካባቢ ንጽህና እንዲሁም የንጽህ ውሃ አቅርቦት ጉዳይ በአካል ጉዳተኞች ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። በተለይ የዚህ ችግር ሰለባ የሆኑ ወገኖችን በገጠር አካባቢ በመኖራቸው መሠረታዊ የሆኑ ግልጋሎቶችን በቀላሉ ማግኘት ባለማቻላቸው ችግሩ የተወሳሰበ እንዲሆን አድርጎታል።
ፖፕሌሽን ሚዲያ ሴንተር ኢትዮጵያ ከተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት (UNICEF) ጋር በመተባበር የ’ዋሽ’ (WASH) ሥራዎችን ላለፉት ሁለት ዓመታት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ማለትም በደቡብ፣ በኦሮሚያ፣ በሲዳማ፣ በጋምቤላ፣ በቢኒሻንጉል ጉሙዝ፣ እና በአፋር ክልሎች በርካታ ሥራዎችን ሲሰራ ቆይቷል። ከዚህም ጋር በተያያዘ የተለያዩ የተግባር መመሪያ አዘጋጅቶ በማጠናቀቅ ላይ ነው። ከእነዚህም መተግበሪያና ማስፈጸሚያ ሰነዶች መካከል 1. ሥርዓተ ፆታ እና ‘ዋሽ‘ 2. አካል ጉዳተኞች እና ‘ዋሽ’፣ እንዲሁም 3. የወር አበባ፣ ጤና እና የንፅህና አጠባበቅ ዋሽ ይገኙበታል።
ፖፕሌሽን ሚዲያ ሴንተር ኢትዮጵያ በዘርፉ የሚስተዋለውን ችግር ለመፍታት ከክልሎቹ እስከ ወረዳ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት ጋር በመሆን ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን በራዲዮ ቶክ ሾው እና ድራማዎች፣ እንዲሁም ማሕበረሰቡን ያሳተፈ የንቅናቄ ሥራዎችን ሲሰራ ቆይቷል። በዚህም የ’ዋሽ’ ፕሮጀክቶች ተግባራዊ በሆነባቸው ወረዳዎች ለውጥ
መታየት መጀመሩን ተቋሙ በወረዳዎቹ ባደረጋቸው የመስክ ምልከታ እና ግምገማዎች ማረጋገጥ ችሏል። ለውጡም በወረዳ ደረጃ ብቻ እንዳይቀር እና እንደ ሀገርም መንግሥት በዘርፉ የሚያከናውናቸው ሥራዎች ቀጣይነት እንዲኖራቸው፣ እንዲሁም በተደራጀና በተቀላጠፈ መልኩ እንዲተገበሩ ይረዳ ዘንድ ከዩኒሴፍ በተገኘ ድጋፍ ሰባት የሚደርሱ ሥርዓተ ፆታ እና አካል ጉዳተኞችን ያካተተ የውሃ ሳኒቴሽን እና ኃይጂን እንዲሁም የወር አበባ ጤናና ንጽህና አጠባበቅ መሠረት ያደረጉ የትግበራ መርጃ ሰነዶችን አዘጋጅቷል።
ሰነዶቹም 1. የሃይማኖት መሪዎች የ’ዋሽ’ መርጃ ሰነድ፣ 2. የጋዜጠኞችና የሚዲያ ፈፃሚዎች የ’ዋሽ’ መርጃ ሰነድ፣ 3. የትምህርት ቤት ‘ዋሽ’ የማሕበራዊ የባሕሪ ለውጥ የትግበራ መመሪያ ሰነድ፣ 4. የሥርዓተ-ፆታ ምላሽ ሰጪ እና አካል ጉዳተኞችን ያካተተ ‘ዋሽ’ የትግበራ መመሪያ ሰነድ፣ 5. አካታች የወር አበባ ጤና እና ንፅህና አጠባበው መመሪያ ሰነድ፣ 6. ሁሉን አቀፍ የማሕበረሰብ ግብረመልስ እና ምላሽ ሰጪ ዘዴ የ‘ዋሽ’ አገልግሎቶች መመሪያ ሰነድ፣ 7. የወር አበባ ጤና እና ንፅህና አጠበበቅ ደህንነቱ የተጠበቀ ነፃ የማረፊያ ሥፍራ መመሪያ ናቸው።
እነዚህ ሰነዶች በፖፕሌሽን ሚዲያ ሴንተር ኢትዮጵያ አስተባባሪነትና ድጋፍ ሰጪነት ከዩኒሴፍ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ የተዘጋጁ ይሁኑ እንጂ፣ ከይዘት ዝግጅት ጀምሮ እስከ ግብዓት አሰባሰብ፣ ብሎም እስከ ማጠናቀቂያው እና ጉዳዩ በሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት እስከ ማጸደቅ እንዲሁም ሥልጠናዎችን እስከ መስጠት ድረስ ከጤና ሚኒስቴር፣ ከትምህርት ሚኒስቴር፣ ከውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ ከሴቶችና ማሕበራዊ ጉዳዮች ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማሕበራት ፌዴሬሽን፣ ከብሔራዊ የዋን ዋሽ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት፣ ከሃይማኖት ተቋማት ተወካዮች፣ ከሚዲያ ተቋማት የተውጣጡ የቴክኒክ ኮሚቴ አባላት የጎላ ሚና ተጫውተዋል። ዶኩመንቶቹ በመንግሥት ደረጃ ያለውን ሥርዓት ጤና ለማጠንከር እና ለአቅም ግንባታ ሥራዎች እንደሚረዱ ይታመናል።
የማስፈጸሚያ ሰነዶቹ ወደ ትግበራው በሚለወጥበት ወቅት በተለይ የጤናው፣ የትምህርት፣ የማሕበራዊው፣ የውሃና ሥርዓተ ፆታ መስክ የ’ዋሽ’ ሥራዎችን በተደራጀና በተቀላጠፈ መልኩ እንዲተገብሩ ይረዳል። ሰነዶቹ በተለይ በአገር አቀፍ እና በክልሎች ደረጃ የሥራ ድግግሞሽ እንዳይፈጠር ከማስቻላቸውም ባለፈ ወጥነትና ቀጣይነት ባለው መልኩ እንዲተገበሩም ይረዳል። መመሪያዎቹ በሚዘጋጁበት ወቅት ሥርዓተ ፆታና አካል ጉዳተኝነትን ያካተቱ መሆናቸው በቀጣይ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚተገበሩ ፕሮጀክቶች ይህንኑ መሠረት ያደረጉ እንዲሆኑም ያስችላሉ። መተግበሪያዎቹ የሕብረተስቡን ተሳትፎ የሚያሳድጉ ከማድረጉም በተጨማሪ ግልጽነት፣ ኃላፊነት እና የተጠያቂነት አሰራሮች እንዲኖሩ ያግዛሉ። ሰነዶቹ እንደ ሀገር የውሃ ሳኒቴሽንና ኃይጂን/ ’ዋሽ’ እና በወር አበባ ጤናና ንጽህና አያያዝ ላይ የታዩ ክፍተቶች እንዳይኖሩም ያግዛሉ ተብሎም ይታመናል።
በዶኩመንቶቹ ላይ ከፌዴራል ጉዳዩ ለሚመለከታቸው የመንግሥት ለሚንስቴር መሥሪያ ቤት ተወካዮች፣ ሁሉም ክልሎች እና ሁለቱ ከተማ መስተዳድሮች፣ የቢሮ ተወካዮች፣ ጋዜጠኞችና የሚዲያ ፈጻሚ አካላት በተለያዩ ዙሮች የተለያዩ ሥልጠናዎች የተሰጡ ተሰጥቷል። በሥልጠናዎቹ ወቅት ክልሎቹ ለአተገባበሩ እቅዶቻቸውን በማዘጋጀት ወደ ተግባር ለመግባት ከስምምነት ላይ ደርሰዋል።
እነዚህን ጠቃሚ ሰነዶች ለማዘጋጀት ከሁለት ዓመታት በላይ የፈጀ ሲሆን፣ ሴቶችና አካል ጉዳተኞች በሚገባ የተሳተፉበት በመሆኑ አፈጻጸሙ ውጤታማ እንደሚሆን ይታመናል። ሰነዶቹን ሥራ ላይ ለማዋል የማስተባበር ሥራው በጤና ሚኒስቴር፣ በውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ በትምህርት ሚኒስቴር፣ በሴቶችና ማሕበራዊ ጉዳዮች ሚኒስቴር፣ በብሔራዊ የዋን ዋሽ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት እና ዩኒሴፍ የሚሰራ ይሆናል።